የኢትዮጵያን ሕዝብ ባንድነት በነፃንትና ብልፅግና ለምስተዳደር የተነሳችሁ የዶ/ር አብይ ቡድኖች !

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ

ከዚህ በፊት ያልታየ፤ ያልተሰማ ታላቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ መመጠን የማይቻል ክብደትና ጭንቀት እንደሚሰማዎት መገምት እችላለሁ። ለጭንቀቱ ሳይሆን ለሕዝቡ ድጋፉና ፍቅሩ እንኳን ደስ አለዎት እላለሁ። ታማኝ በየነ ጎንበስ ብለው እግር ለመሳም ያደረጉት ሙከራ ሃሳብዎንና ለሕዝቡ ያሳዩትን ፍቅርና ኢትዮጵያን እግር ለመሳም እንደነበር ይገባኛል። ግን ይህን ሁኔታ አይቼ እንባዬ ሲመጣ ቶሎ ብዬ ፍርሃት አኮማተረኝ። በዓለም ላይ እንደዚህ ተከብረው በስልጣን መርዝ አውሬ የሆኑ መሪዎች ትዝ አሉኝ። ስልጣንና ገንዘብ መርዝ ናቸው። ያልገዙት ያልለወጡት የሰው ተፈጥሮ የለም። ዉሾች ጠግበው የኢትዮጵያ ህዝብ በረሃብ የሞተበት ስርዓት ሲቀየርና አንጀቱን በገመድ እያሰረ “አገሬ ኢትዮጵያ” ሲል የነበረው ደርግ በመጀመሪያ ህዝቡ እልል ብሎለት ነበር። የንጉሱን ባለስላጥናት እንደበግ አስሮ በሕግ ፊት ሳያቀርብ መረሸኑ “ከሕግ በላይ” መሆኑን ሲያሳይ ነበር ኢትዮጵያ መከራ እንደገባች የገመትነው። ሕግ የማይከበርበት ስርዓት ምን ጊዜም ቢሆን ሰላም አያመጣም።
ዘራፊዎቹ፡ ገዳዮቹ፤ ጨቋኞቹ እንደፈለጉት ሲዝናኑ አንዳንዶቹም ሲሾሙ አገራችን ውስጥ ሰላም አይመጣም።
ፖላንድ በ”ሶሊዳርኖሽች” በሚባለው የትግል መመሪያ የኮሙኒስቱን ስርዓት ከስልጣን ሲያገሉ መጀመሪያ የተመረጠው ጠ/ይ ሚኒስቴር ወፍራም ስረዝ በሚል የይቅርታ ቃል በመግባት በሩሲያ እየተመራ ህዝቡን ሲጨቁን የነበረውን ፓርቲ አባሎች ዝም ብለው ያለጥያቄ ለቀቋቸው። ከላይኛው ስልጣን ዞር ብለው ከስር ያለውን ያስተዳደር ኔትዎርክ የፍርድና የደህንነት ክፍልን ይዘው ህዝቡን ሲያባሉትና ሲበዘብዙት ኖሩ ። የሚያሳዝነው ግን የመጀመሪያው የሶሊዳሪቲ መሪ በሕዝብ የተመረጠው ፕሬዚደንት ቀጥሎም የኖብል ሽልማት የተሰጠው ሰው የኮሙኒስቶቹ ድብቅ ሰላይ መሆኑ ሲገለፅ ነበር። ይህ ነው የ”ይቅርታ” ትልቁ ስህተት። እኔ የፈራሁት ይህ ሁሉ ሕዝባችንን በተስፋ ያሰከረው ምኞት በወሬ እንዳይቀርና ሌላ ያልታሰበ የብሔር መጫረስ እንዳያመጣ ነው።
ይህንን የምጽፈው ላገሬ ያለኝ ፍቅርና ስጋት ሰላም ስላልሰጠኝ ነው።
በፖላንድ የሚገኘው የኢትዮጵያና ፖላንድ ማሕበር በ2003/ም ሲመሰረት ሁሉም ብሔረሰብ ያለበት ኤርትራውያንም የሚሳተፉበት ፖሊቲካ፤ ኃይማኖትና ዘር/ብሔር ሳይል እስከዛሬ ድረስ ተግባብተን ተደምረን ኖረናል። በስርዓቱ አስቀያሚነት ምክንያት ከማንም የፖሊቲካ ፓርቲዎች ሳንጨማመር ተግባብተን ቆይተናል። ከመንግስት ተወካይ ኢምባሲዎች ርቀናል። አሁን ይህ መስሪያ ቤት በደንብ ከፀዳ ብኋላ አብሮ ለመስራት ሙሉ ፈቃደኞች ነን።
ሁሉም እንደሚሉት አምላክ/አላህ ለኢትዮጵያ ምህረቱን አቅርቦላታል አገርና ሕዝብ ወዳጅ መሪም ሰጥቷታል። የተመሰገነ ይሁን። ቀጥሎም ሳይረሳን መሪአችንን ከክፉዎች ይጠብቅልን። አሜን !!