የኢትዮጵያ ሕዝብ ፀሎት እየተሰማ ነው

ተደምሮ ተስማምቶ ተከባብሮ ተፈቃቅሮ መኖርን የጀመርነው “ሰላም” የኢትዮጵያና ፖላንድ ማሕበራችንን ከመሰረትን ከ15 ዓመት ጀምሮ(2003) ነበር። ይህ ለኛ አዲስ ነገር አይደለም። ማሕበራችን የብሔር፤ የሃይማኖት፤ የፖሊቲካ ልዩነት አያወራም፤ አይነሳም። ዋናው ከዛች የፍቅር አገር መምጣታችን ብቻ ነው። ማሕበራችን ውስጥ ኤርትራውያን፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ኦሮሞ፣አማራ ወዘተ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄረ ሰዎች አሉበት። የደርግና የኢሃዴግም አባሎች ሊኖሩበት ይችላሉ። ለኛ ዋጋ አልነበረውም። ግን እከሌ የየት ብሔር ተወካይ ነው ብለው ቢጠይቁኝ መናገር አልችልም። ስለዚህ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ በደረሱበት ችግር ውስጥ በመግባት መተባበርና መረዳዳት የተፈጥሮ ሂደታችን ነው።፡ ስለ ቁሉቢ ገብረኤል ጉዞ ሰምታችሁ ከሆነ ካዲስ አበባ ተነስተው የሚያድሩት አስበ ተፈሪ አሁን ጪሮ የሚባለው ከተማ ነበር። ልጅ ሆኜ አውቶቡስ ጣቤ እየሄድኩ መኝታ የሌላቸውን ሰዎች እየሰበሰብኩ ቤታችን ውስጥ ፍራሽ እያነጠፍን በነጻ እናሳድር ነበር። ይህ መደመር ነበር አዲስ ነገር አይደለም። ከየት መጣችሁ የየት አገር(ክፍለ ሃገር) ሰዎች ናችሁ ብለን ጠይቀን አናውቅም። እንደዚህ መጠየቅ እንዳለም አናውቅም ነበርና። ይህ ንጹህነት ነበር። ንጹሁን ሕዝብ አበላሹት። ይህን ችግር አሁን  የ ዶ/ር አብይ ቡድኖች ሊያስተካክሉት ይሞክራሉና እግዜር ይርዳቸው፤ አሜን፤፡ በዚህ ዓለም ብዙ ኃብታሞች ይኖራሉ። ብዙዎቹ ደስተኛ አይደሉም። በገዛ ኃብታቸው እስረኞች ናቸው። የነቁት ኃብታቸውን ለተቸገሩ መካፈል ጀምረዋል። ይመስገን አምላካችን። እኛን ግን ማን ያለንበት ችግር ዉስጥ አስገባን? ትልቁ ጥያቄ ነው። እንቀበለው የሱ ምስጢር አይታወቅምና። ይህ ክፉ ቀን ያልፋል የተሻለ ነገር ይገጥመናል ብለን እናስብ። ይሳካልን አሜን።